የማህፀን በር ካንሰር (Cervical Cancer)
በአብዛኛው ከከፍተኛ የካንሰር ስጋት ካላቸው HPV (High-Risk Human Papillomavirus) ዓይነቶች የረጅም ጊዜ ኢንፌክሽን ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ነው። የማህፀን በር ካንሰር ቀድመው ከሚታወቁና በቅድመ-ምርመራ በሙሉ ሁኔታ መከላከል ከሚቻሉ የካንሰር አይነቶች አንዱ ነው። ቅድመ-ካንሰር (Pre-cancerous) ለውጦችን በጊዜ በመለየት እና አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ ካንሰር እንዳይፈጠር መከላከል ይቻላል።
ዋና ዋና የማህፀን በር ካንሰር የምርመራ ዘዴዎች (Screening Methods)
የማህፀን በር ካንሰርን እና ቅድመ-ካንሰር ሴል ለውጦችን ለመለየት የሚያገለግሉ ዋና ዋና የምርመራ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፦
- HPV DNA test፦ ለካንሰር ከፍተኛ ስጋት የሆኑትን የ HPV ቫይረስ አይነቶች መኖር እና አለመኖር በላብራቶሪ መመርመሪያ ዘዴ የሚያረጋግጥ ዘመናዊ የምርመራ አይነት ነው።
- Pap smear (Cytology)፦ በማህፀን በር ላይ የተፈጠሩ ያልተለመዱ የሴል ለውጦችን (Cell changes) በማይክሮስኮፕ በመመርመር ካንሰር ከመፈጠሩ በፊት የሚለይ ዘዴ ነው።
- VIA Test (Visual Inspection with Acetic Acid)፦ የ HPV DNA ወይም Pap Smear ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች በአይነ-ቁራጭ የሚደረግ ፈጣን የአሲድ ምርመራ ዘዴ ነው።
የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ በየስንት ጊዜ መደረግ አለበት?
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) አዳዲስ መመሪያዎች እንደሚያሳዩት የምርመራው ጊዜና ቅደም-ተከተል እንደ ግለሰቧ የጤና ሁኔታና አካባቢው በሚገኙ የመመርመሪያ መሳሪያዎች ይወሰናል፦
1. በአጠቃላይ ለሴቶች (General Population)
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የ HPV DNA testን እንደ ዋና የመጀመሪያ ምርመራ ይመክራል። ይህ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ ከ 30 ዓመት ጀምሮ እንደ ሀገሩ የጤና ፕሮግራም መመሪያ መሰረት በየ 5 እና 10 ዓመቱ እንዲደገም ይመከራል።
2. የኤች.አይ.ቪ (HIV) ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ላሉ ሴቶች
የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ በሚገኝ ሴቶች ላይ የማህፀን በር ካንሰር የመያዝ ስጋት ከፍ ያለ በመሆኑ፣ ምርመራው ገና ከ 25 ዓመት ጀምሮ በየአጭር ጊዜ ልዩነት (በየ 3 እና 5 ዓመቱ) እንዲደረግ ይመከራል።
3. የ HPV DNA ምርመራ በሌለባቸው አካባቢዎች
የ HPV DNA ምርመራ በስፋት በማይገኝባቸው የጤና ተቋማት፣ WHO እንደ አማራጭ የ VIA ወይም የ Pap smear (Cytology) ምርመራን በየ 3 ዓመቱ እንዲደረግ ይጠቁማል።
ጠቃሚ ማሳሰቢያ፦
የቅድመ-ምርመራ መመሪያዎች እንደየአገሩ እና በጤና ተቋማት እንደሚገኙ የመመርመሪያ አገልግሎቶች ሊለያዩ ስለሚችሉ፣ በአካባቢዎ በሚገኝ የጤና ተቋም ወይም የማህፀን ህክምና ክፍል በመገኘት የጤና ባለሙያዎችን ማማከርና መመሪያቸውን መከተል ይገባል።
ማሳሰቢያ፦ ይህ መረጃ ለትምህርታዊና ለግንዛቤ ዓላማ ብቻ የተዘጋጀ ነው። ማንኛውም የጤና ጥያቄ ወይም ምልክት ሲኖርዎት በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም በመሄድ ከሀኪም ጋር ይማከሩ።


No comments:
Post a Comment