የመቀመጫ ኪንታሮት (Hemorrhoids) በመቀመጫ ወይም በመጸዳጃ አካባቢ የሚገኙ የደም ስሮች ማበጥና መወጠር ሲሆን፣ እጅግ በጣም የተለመደና ብዙ ሰዎችን የሚያጋጥም የጤና ችግር ነው።
የኪንታሮት ዓይነቶች
ኪንታሮት በዋናነት በሁለት ይከፈላል፦
- ውስጣዊ ኪንታሮት (Internal Hemorrhoids)፦ አብዛኛውን ጊዜ ህመም የለውም፤ ነገር ግን በሚጸዳዱበት ወቅት በጣም ቀይ የሆነ ደም ሊፈስ ይችላል።
- ውጫዊ ኪንታሮት (External Hemorrhoids)፦ ከፍተኛ ህመም፣ ማሳከክ እና ማበጥ ያለው ሲሆን ታካሚዎችን እጅግ በጣም ያሰቃያል።
ለኪንታሮት የሚያጋልጡ ዋና ዋና ምክንያቶች
- በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ረጅም ሰዓት መቀመጥ፦ በተለይ ስልክ ይዞ ገብቶ በመጸዳጃ ቤት ላይ ረጅም ሰዓት መቀመጥ የመቀመጫ ደምስሮች ላይ ጫና ስለሚፈጥር ለኪንታሮት ያጋልጣል።
- የሆድ ድርቀት (Constipation) እና ማማጥ፦ በሚጸዳዱበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ማማጥ።
- በቂ የፋይበር (Fiber) ምግብ አለመመገብ።
- ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት (Obesity)።
- እርግዝና፦ በሆርሞን መለዋወጥ እና በጽንሱ ጫና ምክንያት።
- እድሜ መጨመር፦ የሰውነት ህብረህዋሳት (Tissues) የመለጠጥ አቅም በመቀነሱ።
የኪንታሮት ዋና ዋና ምልክቶች
- ቀይ ቀለም ያለው ደም መፍሰስ
- በመቀመጫ አካባቢ ከፍተኛ ማሳከክ እና ህመም
- የመቀመጫ አካባቢ እብጠት
- የሚለጨለጭ ፈሳሽ (Mucus) መውጣት
ማስታወሻ፦ የመቀመጫ ደም መፍሰስ የሌሎች ህመሞችም ምልክት ሊሆን ስለሚችል ወደ ህክምና ቦታ ጎብኝቶ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
በቤት ውስጥ የሚደረጉ ተፈጥሯዊ ህክምናዎችና መፍትሔዎች
- የፋይበር ምግቦችን በብዛት መመገብ፦ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ ተልባ እና ሲሊየም ሀስክ (Psyllium Husk) በብዛት መመገብ የሆድ ድርቀትን ይከላከላል።
- በቂ ውሃ መጠጣት፦ በቀን ቢያንስ እስከ 2.5 ሊትር ውሃ መጠጣት ሰገራ እንዲለሰልስ ይረዳል።
- የእንፋሎት/የለብ ውሃ ቁጭ ብሎ መዘፍዘፍ (Sitz Bath)፦ ለብ ያለ ውሃ ውስጥ ጥቂት ጨው በመጨመር በቀን 3 ጊዜ ከ10 እስከ 20 ደቂቃ መቀመጥ ህመሙን እና ማሳከኩን በእጅጉ ይቀንሳል።
- የመጸዳጃ ቤት ልማድን ማስተካከል፦ ስልክ ይዞ ወደ መጸዳጃ ቤት አለመግባት እና ያለአስፈላጊ በኃይል አለማማጥ።
- ስፖርት እና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፦ ክብደትን ለመቀነስ እና የአንጀት እንቅስቃሴን ለማፋጠን ይረዳል።

No comments:
Post a Comment